ነሐሴ 3/2017 ዓ.ም–ዞብል ፖስት ዜና!
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ገዳ ልዩ ኮማንዶ የተሰኘ ወታደራዊ ኃይል በአዲስ አበባ ከተማ ሊያሰማራ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።
በከተማዋ ይሰማራል የተባለውና “ገዳ ልዩ ኮማንዶ” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ኃይል የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ መዋቅር ክንፍ ሲሆን፣ በአዲስ መልክ የሚዋቀርና በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ልዩ ስምሪት የሚሰጠው መሆኑ ተነግሯል።
ልዩ የኮማንዶ ኃይሉ ከፌዴራል ፖሊስ እና አዲስ አበባ ፖሊስ ጎን ለጎን በከተማዋ ስምሪት የሚሰጠው ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትን እንዲጠብቅ ይደረጋል መባሉን ለዞብል ፖስት የደረሰው መረጃ ያሳያል።
የኦሮሚያ ክልል ለገዳ ልዩ ኮማንዶ ኃይል የሚሆን የሰው ኃይል መልምሎ መጨረሱን እና ልዩ ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ መረጃውን ለመጽሔታችን ያደረሱት ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ በርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ህንፃዎች ያሉት ሲሆን፣ በስልጠና ላይ የሚገኘው የገዳ ልዩ ኮማንዶ ኃይል ስልጠናውን ሲያጠናቅቅ እነዚህን ተቋማት እንዲጠብቅ ይደረጋል ተብሏል።
የመረጃ ምንጫችን አክለውም፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ መምሪያ መቀመጫውን በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ካደረገ በኋላ አስራ አራት የሚጠጉ ቦታዎችን ለወታደራዊ ካምፕ አገልግሎት እንዲውሉ አጥሮ ማስቀመጡን በመጠቆም፣ የገዳ ልዩ ኮማንዶ ኃይል እነዚህን ቦታዎች እንዲጠብቅ እንደሚደረግ ለመጽሔታችን አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የገዳ ልዩ ኮማንዶ ኃይል ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን እንዲጠብቅ እንደሚደረግ እና በሞጆ እና ናዝሬት ዙሪያ ስምሪት እንደሚሰጠው የመረጃ ምንጫችን ለዞብል ፖስት ገልጸዋል።


